1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፊንላንድ 31ኛዋ የኔቶ አባል ሀገር

ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2015

ፊንላንድ በትናንትናው ዕለት የስሜን አላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ፤ 31ኛ አባል ሀገር በይፋ ሆናለች። ፊንላንድና ስዊድን ባለፈው ዓመት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፍተችውን ጦርነት ተክትሎ የኔቶ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው መቆየታቸው ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/4Pjim
Finland NATO Beitritt Mitglied
ምስል ASSOCIATED PRESS/picture alliance

«ፊንላንድ የኔቶ አባል ሆነች»

 

ፊንላንድ በትናንትናው ዕለት የስሜን አላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ፤ 31ኛ አባል ሀገር በይፋ ሆናለች። ፊንላንድና ስዊድን ባለፈው ዓመት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፍተችውን ጦርነት ተክትሎ የኔቶ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው መቆየታቸው ይታወሳል። ፊንላንድ ከስዊድን ቀድማ የድርጅቱን 30 አባል ሃገራት ይሁንታ በማግኘቷ ነው ከትናንት ጀምሮ የድርጅቱ አባልኗቷ በይፋ የተገለጸው።

 የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ያንስ ስቶልቴንበርግ ብራስልስ  በሚገኘው የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት የሁሉም አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የፊንላንድ ፕሬዝዳንት በተገኙበት በነበረው ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግርም ይህንኑ አብስረዋል።

«የዛሬው ዕለት ፊንላንድን  ወደ ስሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ በሙሉ አባልነት የተቀበልንበት ታሪካዊ ዕለት ነው።» በማለት ለመጀመሪያ ጊዜም የፊንላንድ ሰንደቅ አላማ በዋናው ጽሕፈት ቤት ከሌሎቹ 30 አባል አገሮች ሰንደቅ አላማ ጎን የሚውለበልብ መሆኑን አስታውቀውል። 

Nato Finland Flagge
የኔቶ አባል ሃገራት ሰንደቅ አላማምስል Geert Vanden Wijngaert/AP/picture alliance

ፊንላንድ በዓለማችን ካሉት በተለይም ከበለጸጉት ምዕራባውያና አገሮች በገለልተኘነቷ የምትታወቅና የየትኛም ወታደራዊ ድርጅት አባል ሳትሆን የቆየች ቢሆንም፤ አሁን ግን ይህ አቋሟ የተለወጠ መሆኑን በዚሁ ስነስርአት ላይ የተገኙት ፕሪዝዳንቷ ሚስተር ስዊሊ ኒኒስቶ ባደረጉት ንግግር ይፋ አድርገዋል።

«በታሪካችን የነበረው የወታደራዊ ገለልተኝነት ዘመን ዛሬ አብቅቷል። አዲስ ዘመንና ወቅት ተፈጥሯል።» በማለትም አገራቸው ወደ አዲስ ስርአትና ወታደርዊ ጉድኝት የገባች መሆኑን ገልጸዋል።   

የፊንላንድ ወደ ኔቶ መግባትና ሙሉ አባል መሆን ምን ማለት እንደሆነ ዋና ጸሐፊ ስቶልቴንበርግ ሲናገሩ፤ « ይህ ማለት ከዛሬ ጀምሮ ፊላንላንድ ለደህንነቷና ሉዑላዊነቷ የኔቶን ዋስትና ታገኝለች ማለት ነው። የድርጅቱ ደንብ አንቀስ 5  በአንድ አባል አገር ላይ የተደረገ ጥቃትን በሁሉም አባል አገሮች ላይ እንደተፈጸመ ጥቃት የሚቆጥርና አንዱ ለሁሉም ሁሉም ለአንዱ እንዲቆም የሚጠይቅ ነው በማለት ከእንግዲህ የፊንላንድ ደህንነት የሚረጋገጠው በራሷ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኔቶ ቤተሰቦች ጭምር» እንደሚሆን አስታውቀዋል።  

 ፊንላንድ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ እ እ እ በ1948 ዓም ከ1300 ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር ከምታካልላትና በርዕዮተዓለም  ግን ከምትለያት የያኔዋ ኮሚኒስት ሶቭየት ኅብረት በኋላም ከአሁኗ ሩሲያ ጋር መልካም ጉርብትናን በመፍጠር በገለልተኝነት ለበርካታ ዓመታት በሰላም የዘለቀች አገር በመሆን ትታወቃለች። ሆኖም ግን ባለፈው ዓመት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ፊንላንድን ብቻ ሳይሆን ሌላዋን ገለልተኛ የኖርዲክ አገር ስዊድንንም ወደ ኔቶ እንድትዞር እንዳደረጋት ነው የሚነገረው።   

Finland NATO Beitritt Mitglied
የፊንላንድ እና የኔቶ ሰንደቅ አላማምስል ASSOCIATED PRESS/picture alliance

በፊንላንድ ወደ ኔቶ መግባት ዩክሬንና አሜሪካ ደስታቸውን ሲገልጹ፤ ሌሌች የድርጅቱ አባል አገሮችም ሁኔታው ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ አገሮች ወደኔቶ እንዳይገቡ የሚያደርጉት ጥረት የከሸፈና የማይቻል መሆኑን የሚያሳይ ነው በማለት፤ በዚህም ሩሲያ ትልቅ የዲፖላማሲ ሽንፈት ያጋጠማት መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል ። 

ሩሲያኖች ግን የፊንላንድ ወደ ሩሲያ መግባትና የኔቶ መስፋፋት ሩሲያን የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ የሚያስገድዳትና አካባቢውንም የበለጠ ውጥረት ውስጥ የሚከት እንደሆነ ነው የሚናገሩት።  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የወጣው መግለጫም የፊንላንድ እርምጃ በዓለማችን ሰላማዊና የተረጋጋ በነበረው የስሜኑ የአውሮፓ ክፍል ውጥረት የሚፈጥር ነው በማለት ሞስኮ በአካባቢው በሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ተመጣጣኝ እርምጃ የምትወድ መሆኑን አስታውቋል። የመከካከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሹውጉም በበኩላችው ይህ ሁሉ እርምጃ በአካባቢው ያለውን ግጭት ከሚያባብስ በስተቀር የሚያመጣው አዎንታዊ ለውጥ እንደማያኖር ነው ያሳሰቡት። በእርግጥም ፊንላንድን የመሠሉ ገለልተኛ የነበሩ አገሮች ወደ ኔቶ መግባትና ድርጅቱም መስፋፋቱ ከሩስያ ጋር ያለውን ፍጥጫ የሚያረግብ በዩክሬን እየተከሄደ ያለውን ጦርነትም የሚያበርድ ሳይሆን፤ ይልቁንም እልቂት ውድመቱን ሊያብሰውና ሊያሰፋው ይችል ይሆናል በማለት የሚሰጉ በርካቶች ሆነዋል።  

ገበያው ንጉሤ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ