1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦነግ የአገር ማረጋጋት ጥሪና የመንግሥት አስተያየት

ሰኞ፣ ነሐሴ 1 2015

በኦሮሚያ ክልል ሊፈታ ያልቻለው የጸጥታ ችግር እንዳሳሰበው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አስታወቀ። ኦነግ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የተስፋፋው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ወደ አጎራባች ኦሮሚያ ክልል እንዳይዛመትም አስጠንቅቋል። መንግሥት በበኩሉ ለአገሪቱ አለመረጋጋት ሰላማዊ እልባትን እንደ ቀዳሚ አማራጭ ከመውሰድ ቦዝኜ አላውቅም ብሏል።

https://p.dw.com/p/4Us0H
 Logo Oromo Liberation Front

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የአገር ማረጋጋት ጥሪ እና የመንግሥት አስተያየት

«ኦሮሚያ የፍቅርና የሰላም ቀዬ መሆን ሲገባት ጸረ-ሰላምና ጸረ-ኦሮሞነት መርህን የሚያቀነቅኑ ተፈራርቀውባት ሰላሟን አጥታለች» ሲል መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በክልሉ ሰላም ማስፈን ይገባል ሲል አመለከተ። በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቷል ያለው ውስብስብ የፖለቲካ ሂደትም በኦሮሚያ የዜጎችን ሕይወት ክፉኛ ጎድቷል ያለው ኦነግ፤ ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም በመግለጫው ጠይቋል። የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ኦነግ መግለጫውን ባሁን ወቅት እንዲያወጣ ያስገደደው፤ «በኢትዮጵያ እየተከሰተ ባለው የስርዓት መሸራረፍ እና አለመረጋጋት የዜጎቻችን ደህንነት ስጋት ውስጥ መግባቱ ነው» ብለዋል።

ኦነግ በዚህ መግለጫ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት አገሪቱ መቋጫ በሌለው ግጭትና ጦርነት ውስጥ መግባቷ ከዴሞክራሲያዊ መብትም መጣስ ባለፈ የህልውና ፈተናን ደቅኖ ቆይቷል ብሏል። ፓርቲው በመግለጫ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ፖለቲካዊ ውይይቶች እንዲደረጉ የቀረቡ ጥሪዎችም ተቀባይነት ማጣታቸው አሁን ለሚስተዋለው የከፋ አለመረጋጋት ምክንያት ነው ብሎ እንደሚያምንም ጠቁሟል። ኦነግ በመግለጫው አክሎም አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጎልቶ የተስተዋለው አለመረጋጋት ወደ ኦሮሚያ እንዳይሰፋና የበዛ ቀውስ እንዳይፈጥርም ጥንቃቄ መወሰድ አለበት ብሏል። ቃል አቀዩ አቶ ለሚ ገመቹም፤ «ኦነግ ጥሪ ሲያቀርብበት የነበረውና አሁንም የሚያምነው ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሆነው የውይይት መንገድ መፈለግ ነው» ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ኢትዮጵያ ባለፉት 3-4 ዓመታት እየገፋች ላለው የሰላም እጦትና ያለመረጋጋት መንገድ ለመውጣት ለውይይት ዕድል እሰጣለሁ ከማለት ቦዝኖ እደማያውቅ ተደጋጋሞ ይገለጻል። የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ይህንኑን በማስመልከት ዛሬ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ አለመረጋጋቶች መንግስታዊ ለውጥን ተከትሎ መከሰቱን አስታውሰዋል። «መንግሥት በሆደ ሰፊነት በውጪም የነበሩትን ኃይሎች ጭምር ወደ አገር እንዲገቡ አውድ አመቻችቶ ነበር። ያ በሂደት ውሎ አድሮ በየአከባቢው አለመረጋጋት ፈጥሯል።»

አሁን ላይ አማራ ክልልን ለከፋ የጸጥታ ችግር ዳርጓል ያሉት ክስተትም ከዚህ እንደማይለይ የገለጹት አቶ ከበደ በተለይም ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙ አካላት ትልቅ ስጋት ሆነዋል ነው ያሉት።

 ይሁንና መንግሥታቸው ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ከአገር ሽማግሌ እስከ የሃይማኖት አባቶች በመላክ ሰፊ ጥረት አድርጓል ያሉት አቶ ከበደ፤ አሁን አማራ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ላሉ ችግሮች ወታደራዊ እርምጃዎች የሚወሰዱት የሰላም መንገዱ በር ሲደፈን ብቻ ነው ብለዋል። «የዜጎች እንቅስቃሴ በመገደብ መከላከያ ሠራዊቱ ከቦታ ቦታ እንዳይሄድ በማድረግ የሰላም ጥረቱ ፍሬ እንዳላፈራ በመታየቱ ነው መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አውጆ ዜጎችን ለመታደግ ወደ እርምጃው ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለው።» ያሉት አቶ ከበደ አክለውም በአማራ ክልል አሁን ጎልቶ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ወደ ሌላ አካባቢዎች እንዳይዛመትና ችግሩ እንዳይሰፋም መንግሥታቸው ዝግጅት ማድረጉን አመልክተዋል።

 ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ