1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ባለሞያዎች ጥሪ

ሐሙስ፣ ኅዳር 15 2015

ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በአቅርቦት ችግር ምክንያት የሚሰጣቸው የሕክምና አገልግሎቶች እየቀነሱ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ብቻ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበረ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። አሁን ተፋላሚ ኃይሎቹ የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ዓይደር የሕክምና ቁሳቁስና መድኃኒት የሚያገኝበት ዕድል ይፈጠራል ብለው ይጠብቃሉ።

https://p.dw.com/p/4K0k6
Äthiopien Tigray-Krieg |  Ayder Krankenhaus in Tigray
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የመቀሌው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ባለሞያዎች ጥሪ

በኢትዮጵያ መንግሥትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ህወሓት መካከል  የተፈረመው የሰላም ስምምነት በትግራይ የጤና አገልግሎት ዘርፍ የነበረውን የከፋ ችግር ያቃልላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጤና ባለሙያ ገለፁ። ለስኳር በሽተኞች የሚሆን ኢንሱሊንን ጨምሮ ሌሎች መድኃኒቶችን አሁንም እንዳላገኘ የሚገልፀው በትግራይ ትልቁ የጤና ተቋም ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል፥ አስፈላጊ የሕክምና ግብአቶች በአስቸኳይ ወደ ትግራይ እንዲደርሱ ጠይቋል። በቅርብ ቀናት ዓለምአቀፉ ቀይመስቀል ማሕበርና ሌሎች እርዳታ ሰጪ ተቋማት መድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች የጫኑ መኪኖችን ወደ ትግራይ ማስገባት መጀመራቸውን ያሳወቁ ቢሆንም ካለው ችግር አንፃር ተጨማሪ አቅርቦት እንደሚጠበቅ በሕክምና ባለሙያዎች ተገልጿል።

በትግራይ ጤና ቢሮ እና አጋር ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በጦርነቱ ምክንያት 80 በመቶ የሚሆኑ የትግራይ ጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ውድመት ደርሷቸዋል። በተለይም ከ2013 ዓመተ ምህረት መጨረሻ ወዲህ ባለው ግዜ ደግሞ ከውድመት የተረፉት በትግራይ የሚገኙ የጤና ተቋማት በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት እና መድኃኒት አቅርቦት እጦት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ እንዲሁም አገልግሎት ማቆማቸውን በክልሉ ጤና ቢሮ በኩል ይገልፃል። በትግራይ ትልቁ የጤና ተቋም በመቐለ የሚገኘው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ አብዛኞቹ ጤና ተቋማት በግብአት እጦት ምክንያት ስራ ማቆማቸውን ተከትሎ በየቀኑ በሽዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች እያስተናገደ ይውላል። 

በአይደር ሆስፒታል ተዋጊዎች ሕክምና ሲያገኙ
በመቐለ የሚገኘው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ አብዛኞቹ ጤና ተቋማት በግብአት እጦት ምክንያት ስራ ማቆማቸውን ተከትሎ በየቀኑ በሽዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች እያስተናገደ ይውላልምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በአቅርቦት ችግር ምክንያት በየግዜው የሚሰጣቸው የሕክምና አገልግሎቶች እየቀነሱ እስከ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ብቻ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበረ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። አሁን የሁለት ዓመቱ ጦርነት አብቅቶ፣ ተፋላሚ ኃይሎቹ የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በትግራይ ትልቁ የሕክምና ተቋም ፣ ዓይደር እንደበፊቱ የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት የሚያገኝበት ዕድል እንዲፈጥር የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ይጠብቃሉ። ከሰላም ስምምነቱ 3 ሳምንታት በኃላ አሁንም ወደ ሆስፒታሉ የደረሰ በቂ ግብአት እንደሌለ የሚገልፁት የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶክተር ክብሮም ገብረስላሴ፣ በተለይም ለስኳር፣ ካንሰር፣ ቲቢ፣ ኩላሊት እና ኤችአይቪ በሽተኞች የሚሆን መድኃኒት በአፋጣኝ እንዲመጣ ይጠብቃሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በየቀኑ በርካታ ታካሚዎች ሲያስተናግዱ የሚውሉት የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ዶክተሮች ላለፉት 17 ወራት ደሞዝ ባለማግኘታቸው ለችግር እንደተዳረጉም ይገልፃሉ። ከ3 ሺህ በላይ የሚሆን የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች ለመጨረሻ ግዜ ደሞዝ ያገኘት በ2013 ዓመተምህረት ግንቦት ወር እንደነበር የሚያስታውሱት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶክተር ክብሮም "የፌደራል መንግስት ለረዥም ግዜ በታማኝነት ሲያገለግል ለቆየ የሕክምና ባለሙያ ይድረስለት" ይላሉ።እንደ የትግራይ ጤና ቢሮ መረጃ እስካሁን በትግራይ የሚፈለገው የመድኃኒት አቅርቦት መጠን ከ5 በመቶ አይዘልም። በቅርብ ቀናት ዓለምአቀፉ ቀይመስቀል ማሕበርና የኢትዮጵያው ተመሳሳይ ተቋም መድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ማስገባት መጀመራቸው አስታውቀዋል። ይሁንና ካለው ችግር አንፃር ተጨማሪ አቅርቦት እንደሚጠበቅ በሕክምና ባለሙያዎች ይገለፃል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ