1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፈንቅለ መንግሥት የተደጋገመባት አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27 2015

አፍሪቃ መፈንቅለ መንግሥት የሚደጋገምባት ክፍለ ዓለም ሆናለች። በታሪክ እንደተመዘገበው በተለይ 1960ዎቹ ዓመታት በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መፈንቅለ መንግሥት በተደጋጋሚ ተደርጓል።

https://p.dw.com/p/4Vrec
ፎቶ ከማኅደር፤ በኒዠር መፈንቅለ መንግሥቱን የተቃወሙ ወገኖች ሰልፍ
መፈንቅለ መንግሥት ከተደጋገመባቸው ሃገራት ሱዳን፣ ማሊ፤ ቻድ እና ኒዠር ቀዳሚዎቹ ናቸው። ጊኒ፣ ቤርኪናፋሶ እንዲሁም ሳኦቶሜና ፒሪንሲፔም ወታደራዊው ኃይል ሥልጣን ለመያዝ የመንግሥት ግልበጣ ያካሄደባቸው ሃገራት ናቸው። ፎቶ ከማኅደር፤ በኒዠር መፈንቅለ መንግሥቱን የተቃወሙ ወገኖች ሰልፍ ምስል Sam Mednick/AP Photo/picture alliance

መፈንቅለ መንግሥት እና አፍሪቃ

አፍሪቃ መፈንቅለ መንግሥት የሚደጋገምባት ክፍለ ዓለም ሆናለች። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከጎርጎሪዮሳዊው 1946 ዓ,ም አንስቶ አፍሪቃ ውስጥ 222 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል። እንደመረጃው በመላው ዓለም ለስድስት አስርት ዓመታት በርካታ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው አፍሪቃውስጥ ነው። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ከጎርጎሪዮሳዊው 2020 እስከ 2022 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻም በ11 ሃገራት መንግሥት የመገልበጥ ሙከራዎች መፈጸማቸው ተመዝግቧል። ከ2022 ዓ,ም ወዲህ ባሉት ጊዜያትም አፍሪቃ ውስጥ ከሚገኙ 54 ሃገራት 45ቱ አንዴ ወይም ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ማስተናገዳቸውን ይኽን አስመልክቶ የተካሄደ ቅኝት ያሳያል። የአፍሪቃ ሃገራት ከቅኝ ግዛትነት ነጻ ከወጡ ወዲህ በአማካኝ አንድ ሀገር ውስጥ ቢያንስ ለአራት ጊዜ የመንግሥት ግልበጣ የተሞከረ ሲሆን ሱዳን ውስጥ ብቻ በቅርቡ የተደረጉትን ጨምሮ 17 ጊዜ ድርጊቱ መፈጸሙ ተመዝግቧል።

በታሪክ እንደተመዘገበው በተለይ 1960ዎቹ ዓመታት በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መፈንቅለ መንግሥት በተደጋጋሚ ተደርጓል። አፍሪቃ ውስጥ ከተረጋጋ የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ ይልቅ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለመባባሱም አንድም ዝቅተኛው የኤኮኖሚ እድገት አንድም የጎሳ ግጭትና ውጥረት መባባስ፣ እንዲሁም አምባገነንና ሙሰኛ አገዛዝን የሚመሩ ግለሰቦች ሥልጣን ላይ የሙጥኝ ማለታቸውን በምክንያትነት የሚያነሱ አሉ። እንዲያም ሆኖ በቅርቡ ከዓመት በፊት ከተደረጉት 11 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ሰባቱ ብቻ መሳካታቸው ተመዝግቧል። በእነዚህ ጊዜያትም መፈንቅለ መንግሥት ከተደጋገመባቸው ሃገራት ሱዳን፣ ማሊ፤ ቻድ እና ኒዠር ቀዳሚዎቹ ናቸው። ጊኒ፣ ቤርኪናፋሶ እንዲሁም ሳኦቶሜና ፒሪንሲፔም ወታደራዊው ኃይል ሥልጣን ለመያዝ የመንግሥት ግልበጣ ያካሄደባቸው ሃገራት ናቸው። በወቅቱም የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ አፍሪቃ ውስጥ የመፈንቅለ መንግሥት ወረርሽኝ መኖሩን መናገራቸው ይጠቀሳል። ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ያመለከቱት ጉተሬሽ በቅርቡ የኒዠር በዚህ ሳምንት  ደግሞ በጋቦን በወታደራዊ ኃይሎች የተካሄዱት መፈንቅለ መንግሥታትን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር መግለጫ ሃገራት ተአማኒ ተቋማትን ቢገነቡ እንደሚበጅ አሳስበዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ በኒዠር የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች
በኒዠር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የደረጉ የሀገሪቱ ዜጎች የገዢውን ፓርቲ ጽሕፈት ቤት እስከማቃጠል ደርሰዋል። ፎቶ ከማኅደር፤ በኒዠር የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች ምስል Fatahoulaye Hassane Midou/AP Photo/picture alliance

«በርካታ ሃገራት ሥር የሰደዱ የአስተዳደር ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል፤ ሆኖም ግን ወታደራዊ መንግሥታት መፍትሄ አይደሉም። እንደውም ችግሩን ያባብሳሉ። ቀውሶችን ማስወገድ አይችሉም። ሊያባብሱት ግን ይችላሉ። ለሁሉም ሃገራት ተአማኒ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በመመስረት የሕግ የበላይነትን እንዲያጸኑ እማጸናለሁ።»  

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ይኽን ይበሉ እንጂ ሥልጣን ላይ ያሉ የአፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት እናስተዳድረዋለን ከሚሉት ሕዝብ አይደለም ትዕዛዛቸውን እየተቀበለ በቅርበት ከሚተባበራቸው የጦር ኃይል የሚቃቃሩት የያዙትን ሥልጣን ላለመልቀቅ በሚያደርጉት ጥረት ለመሆኑ የሰሞኑ የጋቦን መፈንቅለ መንግሥት አንድ ማሳያ ነው። ጋቦን አጠቃላይ ምርጫ ያካሄደችው ባለፈው ቅዳሜ ዕለት ነበር። አሁን ከመንበራቸው ተገደው የተነሱት የቀድሞው ፕሬዝደንት አሊ ቦንጎ የሥልጣን ዘመናቸውን ለሦስተኛ ጊዜ ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ በእሳቸውም ሆነ በሀገሪቱ ላይ ጣጣ አስከትሏል። የአሊ ቦንጎ አገዛዝ ቅዳሜ ዕለት ምርጫ የወጣው ሕዝብ ድምጹን እንደሰጠ ወዲያው የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጥ የሰአት እላፊ ደንብ ነው የደነገገው። የአሊ ቦንጎ እና የቤተሰባቸው ዘመነ ሥልጣን ጋቦን ውስጥ ከ55 ዓመታት በላይ ዘልቋል። ረቡዕ ዕለት አሊ ቦንጎ በምርጫው ማሸነፋቸውን ይፋ እንዳደረጉ፤ ያመጹት የጋቦን ጦር ኃይል መኮንኖች በነዳጅ ዘይት ሀብት የታደለችውን ሀገር ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ የገዛው የአንድ ቤተሰብ ሥርወ መንግሥት ማክተሙትን አስታወቁ። ድርጊቱ የአፍሪቃ ኅብረትን ጨምሮ በበርካቶች ተወገዘ። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ የሚያሰጋቸው መንግሥታት አፍሪቃ ውስጥ መኖራቸው እየተነገረ ነው። ከአራት ሳምንታት በፊት ተመሳሳይ ድርጊት ኒዠር ውስጥ ተፈጽሟል። በዴሞክራሲያዊ መንገድ መመረጣቸው የሚነገረው መሀመድ ባዙም ከነቤተሰባቸው በግል ጠባቂዎቻቸው ቁጥጥር ስር ተደርገው ወታደራዊው ኹንታ የሀገሪቱን አስተዳደር መቆጣጠሩን ይፋ ሲያደርግ የኒዢር የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይም ሆነች የአውሮጳ ኅብረት ድርጊቱን አውግዘው በሚችሉት ሁሉ ጫና ለማሳደር ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ቀደም ሲል ማሊ ከዚያም ቻድ ውስጥ የተካሄዱ መፈንቅለ መንግሥታት የአፍሪቃ ኅብረትን እንዲሁም የአካባቢውን ሃገራት ያሰባሰቡ ማሕበራት ያስተላለፉትን ውግዘትና ተቃውሞ ከቁብ አልቆጠሩም። ጋቦንን ጨምሮ በአብዛኛው የፈረንሳይ የቅኝ ግዛት በነበሩት በእነዚህ ሃገራት የሚደጋገመው መፈንቅለ መንግሥት ለፓሪስ ባለሥልጣናት መጥፎ ዜና እንደሆነ የፈረንሳይን ጉዳይ በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው። የፍራንኮ አፍሪቃ ታሪክ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ተባባሪ አርታኢ ቶማስ ቦሬል፤

ፎቶ በቁም እስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋቦን ፕሬዝደንት አሊ ቦንጎ
«እንደእውነቱ ከሆነ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ በምርጫው በኩል ሊደረግ የነበረውን መፈንቅለ መንግሥት አክሽፎታል። ለጋቦን እንግዳ ያልሆነ ሌላ የምርጫ መፈንቅለ መንግሥት ልናይ ነበር። ይኽ ደግሞ በአሊ ቦንጎ በራሳቸው ለሦስተኛ ጊዜ የሚደረግ ነበር፤ በ2009፣ በ2026 አሁን ደግሞ በ2023። በመጨረሻ ግን የጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት ሂደቱን አቋረጠው።» የፖለቲካ ተንታኙ ቶማስ ቦሬል። ፎቶ በቁም እስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋቦን ፕሬዝደንት አሊ ቦንጎ ምስል TP advisers on behalf of the President's Office/AP Photo/picture alliance

«ለፈረንሳይ ባለሥልጣናት ይኽ መጥፎ ዜና ነው፤ ምክንያቱም የፈረንሳይን የአፍሪቃ ፖሊሲ በስፋት ለመቃወም መንገድ ይከፍታል። በጥንቃቄ ልንመለከተው የሚገባው ደግሞ የዚህ ውጤት ጋቦን ውስጥ የፈረንሳይ ተጽዕኖ እንዲቀንስ ማድረጉን ነው።»

እንደ ቶማስ ቦሬል ከሆነም ጋቦን ውስጥ የተከናወነው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ቢሆንም፤ ሰሞኑን የተካሄደው የሀገሪቱ ምርጫም ሌላ መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድበት ተሞክሯል።

«እንደእውነቱ ከሆነ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ በምርጫው በኩል ሊደረግ የነበረውን መፈንቅለ መንግሥት አክሽፎታል።  ለጋቦን እንግዳ ያልሆነ ሌላ የምርጫ መፈንቅለ መንግሥት ልናይ ነበር። ይኽ ደግሞ በአሊ ቦንጎ በራሳቸው ለሦስተኛ ጊዜ የሚደረግ ነበር፤ በ2009፣ በ2026 አሁን ደግሞ በ2023። በመጨረሻ ግን የጦር ኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት ሂደቱን አቋረጠው።»

ከሥልጣን በኃይል የተወገዱት አሊ ቦንጎበርካቶች በተፎካከሩበት ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን አውጀው ነበር። አፍሪቃ ውስጥ ከምርጫ በኋላ በውጤቱ ተአማኒነት ላይ መጋጨት የተለመደ መሆኑን የሚናገሩት በቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ጉዳዮችን የሚመለከተው ክፍል የዋሽንግተን ቢሮ ዳይሬክተር ቲሲኬ ካታምባላ ምንም እንኳን አፍሪቃውያን ወታደራዊ አስተዳደርን ባይደግፉም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመኖር ተስፋ ያስቆርጣቸው በርካቶች አምባገነኖች ሥልጣን ላይ ከሚሰነብቱ በሚል እንዲህ ያለውን እርምጃ ወደመደገፉ እንደሚያዘነብሉ ይናገራሉ። ዴሞክራቶች ሊሆኑ የሚገባቸው መሪዎች ለዴሞክራሲ ሕጎች አለመገዛታቸው ሰዎች ከዚህ ሥርአት ምን አገኛለሁ የሚል ግራ መጋባት ውስጥ እንደከተታቸውም ያስረዳሉ። የመሪዎች ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል ትርጉም ያለው ሥራ አለመሥራትም ዜጎች ስጋት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ሌላው አፍሪቃ ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት እንዲደጋገም ምክንያት እንደሆነ በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር የሆኑት ራሚ አዲኮያ ያመለክታሉ። ከአፍሪቃ 54 ሃገራት ቢያንስ 27 የሚሆኑት በዓለም እጅግ ዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ከሚገኙ 30 ሃገራት መካከል መሆናቸው የተመድ የሰብአዊ ልማት መዘርዝር ያሳያል። በተለይም በተፈጥሮ ሃብት መታደላቸው የሚነገርላቸው አብዛኞቹ የምዕራብ እና የማዕከላዊ አፍሪቃ ሃገራት የብልጽግናቸው ውጤት በተራው ዜጋ ኑሮ ውስጥ ያመጣው ለውጥ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ በመንግሥታቱ ቅር በመሰኘቱ መፈንቅለ መንግሥቱን ወደመደገፍ እንዲያዘነብል እንደሚደርገው እየታየ ነው።

Niger | Demonstration von Putschisten in
ምስል Balima Boureima/picture alliance/AA

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ዘገባና ትንታኔ