1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኔቶ ለዩክሬን ተጨማሪ ጦር መሣሪያ ለማቀበል ወሰነ

ሐሙስ፣ የካቲት 9 2015

የዩክሬን ሩስያ ጦርነት የሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO)አባል ሃገራትን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳስቧል። አንድ ዓመት ሊደፍን በተጠጋው ጦርነት ሩስያ በምሥራቃዊ ግንባሮች ድል እየተቀዳጀች መሆኑን በመናገር ላይ ናት። ሁኔታው ያሳሰባቸው የኔቶ አባል ሃገራት ባለፉት ሁለት ቀናት በብራስልስ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ተቀምጠው ውሳኔ አሳልፈዋል።

https://p.dw.com/p/4NatH
Brüssel Treffen NATO-Verteidigungsminister | Stoltenberg Generalsekretär
ምስል KENZO TRIBOUILLARD/AFP

ጦርነቱ ኔቶንም አስግቷል

የዩክሬን ሩስያ ጦርነት የሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል ሃገራትን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳስቧል። አንድ ዓመት ሊደፍን በተጠጋው ጦርነት ሩስያ በምሥራቃዊ ግንባሮች ድል እየተቀዳጀች መሆኑን በመናገር ላይ ናት። ሁኔታው ያሳሰባቸው የኔቶ አባል ሃገራት ባለፉት ሁለት ቀናት በብራስልስ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ተቀምጠው ውሳኔ አሳልፈዋል። በውሳኔያቸውም ለዩክሬን ተጨማሪ ጦር መሣሪያ በአፋጣኝ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጠዋል። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ያንስ ሽቶልቴንበርግ፦ «ፕሬዚደንት ፑቲን ዩክሬን ውስጥ ድል ከተቀዳጁ ያ ለዩክሬን እጅግ አሳዛኝ ነው» ብለዋል። ያም ብቻ አይደለም ዋና ጸሐፊው፦ «ለእኛም አደገኛ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።  

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዓባል አገሮች የመከላከያ ሚኒስትሮች፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በብራስልስ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ባካሄዱ ስብሰባ፤  የድርጅቱን የመክላከያ ብቃት ለማሳደግና ለማጠናከር የሚያስችሉ ርምጃዎችን ለመውስድና ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሣሪያና ተተኳሾች ርዳታዎችን በብዛትና በፍጥነት ለማድረስ ወስነዋል። የሰላሳዎቹ የኔቶ አባል አገሮችና የሌሎች ሀያ ዩክሬንን ለመርዳት ክድርጅቱ ጋር የተጣመሩ ሀይሎች ሚኒስትሮች በጋራ የተሰበሰቡት፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የተጠናከረ ጥቃት ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሆነችና፤ ዩክሬን ባንጻሩ ቃል የተገባላትን የጦር መሳሪያ በጇ ስታስገባና እንደውም የተተኳሽ እጥረት እንዳጋጠማት እየተገለጸ  ባለበት ወቅት ነው።፡ በዩክሬን እይተካሄደ  ያለው ጦርነት በአውሮጳ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ያልታየ  አውዳሚ  ጦርነት እንደሆ ነው በብዙዎች እየተገለጸ ያለው። ያም ሆኖ አሁንም የሰላም ጭላንጭል እየታየ እንዳልሆነና ይልቁንም ሩሲያ ጥቃቷን አጠናክራ የቀጠለች መሆኑን የገለጹት  የኔቶ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ያንስ ስቶልቴንበርግ፤ የሚኒስትሮቹን ስብሰባ ትኩረትና ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች በጋዚጣዊ መግለጫቸው አብራርተዋል፤ “ ለዩክሬን  የሚሰጠውን እርዳታ ማጠናከርና ማሳደግ፤  የመከላክል ዓቅማችንና ብቃታችን በአስፈላጊው ሀይልና ትጥቅ እንዲገነባ ማድረግ፤ የወታደራዊ መሰረታዊ ልማቶችን ማጠናከርና ከእንዱስትሪዎቻችን ጋር ማጣመር” የመሳሰሉት ዋናዋናዎቹ ውሳኔ የተላለፈባቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ገልጸዋል። 

Brüssel Treffen NATO-Verteidigungsminister | Stoltenberg Generalsekretär
የዩክሬን ሩስያ ጦርነት የሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ጸሐፊ ያንስ ሽቶልቴንበርግምስል Valeria Mongelli/Zuma/IMAGO

ዋና ጸሐፊው፤ ዩክሬን በጦርነቱ የምትጠቀመው የተተኳሽ መጠን  አባል አገሮች ከሚያመርቱት በላይ በመሆኑ ይህንን ክፍተትና ዕጥረት ለማሟላት የመሳሪያ እንዱስትሪዎችን ማንቀስቀስና አዳዲሶችም እንዲከፈቱ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሚኒስትሮቹ ለዩክሬን ባስቸኳይ የተተኳሾችና የሎጂስቲክስ አቅርቦት እንዲደርስ መስማማታቸውን  ያወደሱት ዋና ጸሐፊ ስቶልቴንበርግ፤ የኔቶን የመከላከል አቅምና ብቃት ለማጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ የሆኑባቸው ምክኒያቶች፤ «የሩሲያ የጦረኝነት ባህሪ፣ የአሸባሪዎች የጥቃት ስጋትና ከቻይና እየተቃጡ ያሉ ፈተናዎች ናቸው» በማለት፤ ይህም ምን ያህል ዓለም በአደገኛ ሁኒታ እንዳለች የሚያሳይ ነው ብለዋል። ከዚሁ ጋርም ሚኒስትሮቹ የመሳሪያ እንዱስትሪዎቻቸውን ማጎልበትና አዳዲሶችንም ማቋቋም እንደሚያስፈግ እንዲሁም የመከላከያ በጅታቸውን ከጠቅላላ ገቢያቸው ቢያንስ ከሁለት ከመቶ በላይ ማሳደግ እዳለባቸው መስማማማታቸው ተገልጿል። 

የኔቶ አባል አገሮችና አጋሮቻቸው እስካሁን ለዩክሬን በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደረዱ የሚገለጽ ሲሆን፤ አንድ መንግስታዊ ያልሆን የጀርመን  ድርጅት እንደገለጸው፤ የኔቶ አባል አገሮች ባለፈው አንድ አመት ብቻ ለልዩክሬን 75.2 ቢሊዮን ዩሮ የፋይናንስ፤ ሰባዊና ወታደራዊ እርዳታ ለግሰዋልል። ይሁን እንጂ ለዩክሬን የሚሰጠው እርዳታና በገፍ እየቀረበ ያለው የጦር መሳሪያ፤ ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም ከማስገደድና ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ ይልቅ፤ የጦርነቱ አድማስ እንዳያሰፋውና እልቂት ውድመቱም እንዲጨምር እንዳያደርገው  ያሰጋል ነው የሚባለው። በኔቶው ስብሰባ የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስተር ሚስተር ሊዮድ ጀምስ ኦውስቲን እንደሚሉት ግን ፤ የኔቶና አጋሮቹ እምንት፤ የዩክሬንን አቅም በሁለንተናዊ መልኩ መገንባትና ማሳደግ ከተቻለ፤ የጦርነቱ ሁኒታ እንደሚለወጥ ነው። «አላማችን ለዩክሬኖች ተጨማሪ አቅም በመሰጠትና በመርዳት በጦርነቱ አጥጋቢ ውጤት እንዲያገኙና ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል ነው» በማለት ይህ ከሆነ ዩክሬኖች በጦርነቱ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት እድል እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

NATO Treffen Brüssel Lloyd Austin
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስተር ሚስተር ሊዮድ ጀምስ ኦውስቲን ምስል AP

ሩሲያ ምዕራባውያን ለዩክሬን በገፍ የጦር መሳሪያ በማቅረብና በመርዳት የጦርነቱ አካል ሁነዋል በማለት ከመክሰስ አልፎ፤ እየደረሰ ላለው እልቂትና ውድመት ተጠያቂዎችም እንደሆኑ ትገልጻለች። በእርግጥም ኔቶ ይህን ያህል መሳሪያ እያቀረበና ተዋጊ ጀቶችንም ለማቅረብ እያሰበ ከሆነ፤ የጦርነቱ አካል አልሆነም ማለት ይቻላል ወይ? ተብለው የተጠይቁት ዋና ጸሀፊ ስቶልቴንበርግ “ ኔቶም ሆነ የኔቶ አጋሮች የጦርነቱ አካል አይደሉም። እያደርግን ያለነው እራሷን እየተካላከለች ያለችውን ዩክሬንን መርዳት ነው። ይህን የማድረግ መብትም አለን በማለት የሚቀርብባቸውን ክስ አስተባብለዋል። 

የውሮጳ ኅብረትና ኔቶ ዩኪሬንን ከመርዳት ባለፈ በሩሲያ ላይ በርካታ የማዕቀብ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሶሞኑን ደግሞ አስረኛውን የማዕቀብ ውስኔ ለማሳለፍ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ እተገለጸ ነው። በተጨማሪም  ጦርነቱ የተጀመረበት የዛሬ ሳምንት ዓርብ በፈረንጆ  የካቲት 24 ዋዜማም የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያን የሚያወግዝ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ገበያው ንጉሤ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ